Created on: 03 May 2025
Description
በየዓመቱ “የፋሲካ፣ የትንሣኤ በዓል” እየተባለ በደመቀ መልኩ በዓለማችን ላይ ይከበራል። ክርስትያኖችም ከበዓሉ ባሻገር በዜማ፣ በውዳሴ፣ በአምልኮ፣ ጌታን በማሰብ ዘወትርም ባይሆን ይዘክሩታል። የምዕራቡ ዓለም ሊቃውንት ትምህርቱ ሕጸጽ እንዳለበት በማስመሰል ተአማኒነት የጎደለው ነው በማለት በመጽሐፍት፣ በመጽሔቶች፣ አልፎም በማኅበራዊ ገጽዎች ላይ ቅዋሜያቸውን ይሰነዝራሉ። አክራሪ ይሁዲዎች እና ሙስሊሞች ትምህርቱ መሠረት የለውም ይላሉ። መጸሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር አፈዎተ ቃል እንደ መሆኑ መጠን የጌታን ትንሣኤ አስረግጦ ያስተምረናል።ትንሣኤ ሙታን የክርስትና መሠረት እምነት ነው። በመሆኑም ትምህርቱን አጥርተን ማወቅ፣ ለሌላውም ማሳወቅ በተለይም ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ዋንኛው ሥራቸው ሊሆን ይገባል።በዘመናችን ብዙ ክርስቲያኖች በመናፍቃውያን ትምህርት እየተሳቡ፣ ወደ እነዚህ ድርጅቶች እንደተወሰዱ በጥናት ተደርሶበታል። የትንሣኤ ሙታን ትምህርት በቅጡ መረዳትና ማወቅ ለክርስትናም ሕይወት ቱርፋቱ ላቅ ያለ ነው። የድል አድራጊ ሕይወት በዚህ ምድር እንዲኖረን ያስችለናል። ተስፋችንን ሰንቀን የጌታን መምጣት እንድንጠባበቅ ያግዘናል። ድካማችን ይቀርፋል፣ ሃዘናችን ይቀንሳል፣ ወንጌላችን ይስፋፋል። ስለ መዳናችንም እርግጠኞች እንሆናለን። አሳዛኙ ግን፣ በየምስባኩ የትንሣኤ ሙታን ትምህርት አንድም ተወረግርጎ፣ አሊያም ብልጭ ድርግም እያለ በመንፈቅ፣ ካልሆነም በዓመት አንዴ ጊዜ የሚሰማ ርእስ ሆኑዋል። አማኒያንም ትምህርቱን በተመለከተ የጠራ እውቀት እንደሌላቸው በርካታ ጥናቶች በዋቢነት ቀርበዋል።ሀልዎተ እግዚአብሐርና ኢመዋቲነት (immortality) የሰው ልጆች በዐጸደ ሥጋ ለመኖር የሕይወት ትርጕም የሚነቅሱባቸው የመቼም ጊዜ መሻታቸውና ፍላጎታቸው ነው። የሰው ልጅ በድኅረ ዘመናዊ እውቀቱ ከሞት በኋላ ሕይወት የለም ቢልም፣ ውስጣዊ ማንነቱ በነጻነት እንዲኖር አያደርገውም። ትንሣኤ ሙታን ከሌለ የዛሬ ተድላና ደስታ የወረሰን “ዛሬን እንብላ፣ እንጠጣ ነገም እንሞታለን” የምንል ምስኪኖች ነን። የሕይወት ትርጉም የጠፋብንና ያለ ሉጓም የምንከፍ አሳዛኞች ነን። “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፣ እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም ፥ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን፥ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስም አልተነሣም፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኋጢአታችሁ አላችሁ።እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋል። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” (1 ቆሮ. 15፥13-19) ኢየሱስ ክርቶስን እግዚአብሔር አብ ከሞት ካስነሳው፣ አምላካችን ሞትን ድል የነሣ መሆኑን ይበልጥ እንረዳለን። ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩት ትምህርት ትክክል መሆኑንም እናውቃለን።ጌታ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሣ እኛንም እንደምንነሣ በእርግጠኝነት እንመሰክራለን። መጻኢውም ተስፋ እውነት እንደሆነ እናበስራለን በዚህ አስተምህሮ ዙሪያ ዊልያም ሌን ክሬግ፣ ሚሻኤል ሊኮና፣ ኤ.ኤን. ራይት፣ ጂ. አር. ሐበርማስ፣ሞርላንድ፣ በመጨረሻም ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ ዳጎስ ያሉ መጻሐፍትን አስነብበዋል። የትንሣኤን ትምህርት ማወቅ፣ ጌታ አምላክነቱን፣ ለሰው ልጅ መሞቱንና ትንሣኤ ሙታን መኖሩን አጉልቶ የሚያሳየን ነው። ሞቶ ከቀረማ፣ ኃጢአታችን ዛሬም ይቅር አልተባለም። ሞትም፣ ኃጢአትም ድል አልተነሱም ማለት ይሆንብናል። ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ከሚያመለክቱ ማስረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን እነሆ፥ 1. የጌታ መቃብር ባዶ ነበር፣ 2. አራቱም ወንጌላት ጌታ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፣ 3. ኢየሱስን ይከተሉ የነበሩ ሴቶች መቃብሩ ባዶ መሆኑን አረጋግጠዋል። አንዳንዶችም በ መላእክት ጭምር ተረጋግጦላቸዋል፣ኢየሱስንም አግኝተውታል፣ 4. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣና እንዳገኙትም ተናግረዋል፣ 5. ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣ ደቀ መዛሙርቱ አስተምረዋል፣ 6. ከሞት ባይነሣ ኖሮ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሕይወትን በሚያስከፍል መሥዋዕት ውስጥ መግባት ባልኖረባቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በእርግጥም ጌታ መነሣቱን አምነው ሰብከዋል። የመጀመርያ ትምህርታቸው ያጠነጠነውም በትንሣኤ ዙሪያ ነው። 7. ሐዋርያው ጳውሎስ ድንገት መለወጡ ጌታ በመነሣቱ የተነሳ ው። ኢየሱስ፣ ጳውሎስን በደማስቆ መንገድ ላይ አገኘው። ሐዋ. 6 ይመልከቱ 8. ተጠራጣሪው ያዕቆብ ድንገት መለወጡ አንደ ማስረጃ ይቀርባል። ጌታ ባይነሣ ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ (የጌታ ወንድም) አያምንም ነበር፣ 9. ክርስትና በኢየሩሳሌም መስፋፋቱ፣ ቤተ ክርስቲያን መጀመሩ፣ 10. በተለያዩ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ተመሠርቷል የሚሉ ይገኙበታል። የጌታችን ኢየሱስ ከሞት መነሣት ከጻድቃን የወደፊት መነሳት ጋር የተቆራኘ፣ የተዛመደ፣ የማይነጣጠል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል።2 ቆሮ. 4፥7፤ 5፥10 ፤ሐዋ. 4፥2 ይመልክቱ። ለውይይት ያህል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣው በሥጋው ወይስ በመንፈስ? መልካም ጥናት