Created on: 25 April 2025
Description
ገጽ ለገጽ የሮሜ መልእክት ምዕራፍ ሰባት ጳውሎስ ምን እያለን ነው? April 25, 2025 የሮሜ መልእክት ምዕራፍ ሰባት አንድምታ ለዘመናት ልዩ ልዩ አተያይ ከአባቶችና ከሊቃውንት ዘንድ ጋብዟል። ጳውሎስ ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ ስድስት ድረስ ደርዝ በተሞላው ወጥነት ካብራራና ከገለጸ በኋላ ፣ የሮሜ መልእክት እንደ አጀማመሩ ባለመቀጠሉ ብዙዎችን አደናግሩዋል፤ መነጋገርያም ሆኑዋል። ምዕራፉ ሕግና ኃጢአትን ጎን ለጎን አሰልፎ፣ በማነጻጸር የሁለቱን ፍልሚያ እንድናይ አድርጎናል።በዐውዱ ከቀረበው መንደርደርያ ተምሳሌት ጀምሮ እስከ „እኔ“ እስከሚለው ተውላጠ ስም ድረስ ብዙ እንድናስብና የተለያዩ እይታዎችን እንድናስተናግድ ምክንያት ሆኑዋል። ታዲያ ማንኛው አመለካከት ትክክል ነው? ምዕራፉ ሰባት የቅደም ተከተል ችግር ይኖርበት ይሆን? ከሆነስ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምዕራፉ ስፍራውን ጠብቆ የመጣ ከሆነ ሥነ አፈታቱ እንዴት ነው? ለምንስ የአመለካከት ልዩነት ተፈጠረ? ሕግ መልካም አይደለምን? “የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና፣ ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም።” ቁ.15 “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና፣ ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።” ቁ. 19፥ 20 “እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” ቁ. 24 ኤሪሽ ሞርሆፈር የተባለ ጀርመናዊና ሰመ ጥር የነገረ መለኮት ሰው “የሥጋና የመንፈስ ውጊያ በጳውሎስ “ በሚለው መጽሐፉ የጥንት ክርስቲያኖች በጉዳዩ ላይ ሁለት አመለካከት እንደነበራቸው ይነግረናል። 1. ክፍሉ የሚያብራራው ዳግም ልደት ስላላገኘ ሰው ነው። ሔራኔዎስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን አባት ይህንኑ በመደገፍ ማብራሪያ ሰጥቷል።። ሌላው የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ አውግሲጢኖስም በመጀመርያ ይህንን እሳቤ ያራመድ እንደነበር ይታወቃል፤ አድሮ ውሎ ግን አቋሙን ቀይሩዋል። 2. ሐዋርያው ጳውሎስ ሰቆቃ የሆነበትን የእራሱን የዳግም ልደት ሕይወትና የሌሎችንም አማኒያን ሁኔታ በማዳምር ገልጿል የሚሉ ወገኖች አሉ። አውግስጢኖስ ይህንን ሃሳብ በመደገፍ “የውርስ ኃጢአት” ያስከተለው የሥጋ ውጊያ ነው ይለዋል። ለብዙ ዓመታት ይህ አስተምህሮ በከፍታ የቆየ ቢሆንም፣የ humanistic እንቅስቃሴ ሲጀምር ግን በምዕራቡ ዓለም መቀዛቀዝ ጀመረ። በዚሁ የተነሳ፣ ክፍሉ የሚያሳየን ከክርስቶስ በፊት ስለነበሩ ሰዎች እና ያለ ክርስቶስን የሆኑትን የሚያመለክት ነው ማለት ጀመሩ።ይሁን እንጅ በዘመነ ተሃድሶ የአውግስጢኖስ ትምህርት በተሃድሶ መሪዎች ዳግም መቀንቀን ተጀመረ። “እኔ” የሚለው አንደኛ መደብ ተውላጠ ስም ለሙግት ዐቢይ ምክንያት መሆኑ በዚህ አንቀጽ ታሳቢ ተደርጉዋል። ብዙ ሊቃውንትም ጉዳዩን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማጣቀስ የተለያየ ሃሳቦችን ሠንዝረዋል።ግራንት ኦስቦርን አንዱ ናቸው።ኦስቦርን የሐዲስ ኪዳን ፕሮፌሰር ናቸው።“እኔ“ን በተመለከተ አራት አተያየቶች መኖራቸውን ዘግበውልናል። 1. ግለ ታሪክ ሐዋርያው ጳውሎስ የልጅነቱንና የፈሪሳዊ ሕይወት ዘመኑን ሕግና ኃጢአትን አስመልክቶ ያሳለፈውን ገጠመኝ ዘክሮልናል። ምንም እንኳ ሕጉ ቅዱስ፣ ጽድቅ የተሞላውና በጎ ቢሆንም፣ ትእዛዛቱን አሟልቶ ለመፈጽም ከቶም አለመቻሉን ከልምዱ ነግሮናል።ስለሆነም የማይወደውን ሁሉ ያደርግ ነበር።ኃጢአት አድርቶበት እንደነበር ገልጾልናል። 2. የአዳም ልምምድ በተለይም ቁ. 7-12 ይሁንኑ ያመለክታል የሚሉ አሉ። አዳም በኤደን ገነት የነበረውን ልምምድ አብክሮ ያሳያል የሚሉም አሉ። 3. እስራኤል እስራኤል ሕግን ከመቀበሏ በፊትና ከተቀበላችም በኋላ ያሳለፈችውን ልምምድ ይጠቁመናል። ቅደመ ሕግ እና ድኅረ ሕግ በተመለከተ እስራኤል ያሳለፈችውን ገጠመኝ ቁልጭ አድርጎ አቅርቦልናል። ኬዜማን እና ራይት የተባሉ ታዋቂዎች በዚህ ረገድ የሰጡትን አስተያየት መጥቀስ ይቻላል። 4. የሰው ዘር ሁሉ “እኔ “ ተብሎ የተጠቀሰው የሰው ዘርን ሁሉ ይመለከታል። በተለይ ቁጥር ሁለትን ለመቀበል አደጋች ነው የሚል ግምት አለኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምዕራፍ ሰባት የዳነውንና ያልዳነውንም ሁሉ ያካትታል የሚሉ አስታራቂ አስተያየት ሰጪ ወገኖች ተፈጥረዋል። ሕግ በመሠረቱ መልካም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም ይመልሳል።” (መዝ.19፥7 ) “በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ ፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው።”(መዝ፣ 119፥1) በተለይም መዝሙር 19 እና መዝሙር 119 ሕጉ ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነ ይነግረናል። ሕጉ ከማርና ከማር ወለላም ይልቅ ይጣፍጣል፣ ሕጉ የእግራችን መብራት ነው።ሕጉን ስናውቅ ፥ - ኅጢአተኛ መሆናችንን ግልጽ ይሆናል፣ - የእግዚአብሔር ቁጣ በላያችን ላይ እንዳለ ያስያየናል፣ - በፍርድ ሥር መሆናችንን ያስታውቀናል፣ - የሞት ፍርድ እንዳለብን ይነግረናል፣ - ሥጋዊ ምኞታችን አጉልቶ ያሳየናል፣ - ሕጉ በኃጢአት ላይ መፍረዱን እናውቃለን፣ በአጠቃላይ ሕጉ ደካማ እንደሆንና ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመዳን ቤዛ እንደሚያስፈልገን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።ታዲያ “እኔ” የሚለው ተውላጠ ስም ማንን ይውክላል? በፕሮፌሰር ጆን እስቶት መሠረት አራት አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። 1. የጳውሎስ የልጅነት ዘመን በተለይም ከአሥራ ሦስት ዓመት ጀምሮ ያለውን ሕይወት ገጠመኝ ያሳያል፤ 2. ፈሪሳዊውን ጳውሎስ ያመለክታል 3. ጳውሎስ አዳምን ተላብሶ “እኔ” ይላል፤ የአዳም ልምምድ በቁ. 7-11 እና በዘፍ. 2-3 ተነጻጽሮ ቀርቧል፣ 4. “እኔ” ነት እስራኤል ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ገና ከመነሻው የባልና ሚስት ትዳር በሕግ ጸንቶ አንዳለ ይነግረናል። ባል ሲሞት ሚስት ከሕጉ ነጻ ነች። ይህች ሴት የወደደችውን ዳግም ልታገባ መቻሏን ይነግረናል። ከቁ:1-4 ያለውን እንደምን እንፍታው? ሀ. እናመሳጥረው? አመስጥሮት ትርጓሜ.....allegorical interpretation ባልና ሚስት የሚለው ውስጠ ወይራ ትርጉም አለውን? ለ. የቁም ትርጉም? ሐ. ሚድራሽ ትርጓሜ? መ. አምሳላዊ ትርጓሜ......typological interpretation …..ሌሎችም አሉ። የትኛው ይረዳናል? ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ መረዳታችን ከፍ ያደርገዋል፣ ይበልጥም ምዕራፉን እንድናጠናው ያግዘናል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ለመረዳት ይጠቅመናል። አንባቢያን መልሱ ለማግኘት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የበኩላችሁን ምርምርና ጥረት እንድታደርጉ አሳስባችኋለሁ። መልካም ጥናት! Dr. Gezahegn Bekele, Ethiopian Evangelical Church Bonn