Created on: 30 December 2024
Description
ኢየሱስን ማን ይሉታል? ይህንን ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን ጠይቆ ነበር። “ኢየሱስ ፊልጶስ ቄሣርያ ወደተባለው አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን `ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?`” (ማቴ. 16፥13 መደበኛው መጽሐፍ ቅዱስ) ብሎ ጠየቃቸው። በተለይም በምዕራቡ ዓለም የጌታ ልደት (ገና) በአል ሲቃረብ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች ፣ ሊቃውንት ጭምር ኢየሱስ ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሙከራ ያደርጋሉ። ብዙዎቹ በምናባቸው ያሰሉትን፣ ሌሎች ስሜቶቻቸው የነገሯቸውን በማካተት አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላሉ። በአንድ ወቅት የነገረ መለኮት እውቁ የኤን. ቲ. ራይት ባልጀራ በኬንያ ላሉ ተማሪዎች ስለ ኢየሱስ (the quest for historical Jesus) ሲያስተምሩ ፣ ጀርመኖች በ 18ኛው እና በ 19ኛው ክፍለ ዘመን ኢየሱስ ስለ መኖሩ እንኳ ተጠራጥረዋል በማለት ተማሪዎችን ይነግሯቸው ጀመር። ከተማሪዎች አንዱ “መምህር ሆይ ጀርመኖች ኢየሱስ ከጠፋብቸው ለደንታቸው ነው፤ እኛ ግን መኖሩን እናውቃለን፤ እናምነዋለን፤ እንወደዋለን፣ እናመልከዋለን” በማለት መለሰ። ይሁን እንጂ ዛሬም ሆነ ጥንት ኢየሱስን በሚመለከት የሚቀርቡ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎች ፣ ክርክሮች መቋጫ አላገኙም። ሁሌም ኢየሱስ አነጋጋሪ ሆኖ ይቆያል። አንዳንዶች ደግሞ ስሙን ጨርሶ ለመስማት አይፈልጉም። ሰይጣንም ስሙ ባይነሳለት ይወዳል። መቼ ያለ ምክንያት! የሳልኼሽን አርሚ (Salvation Army) መሥራች የሆኑት ዊሊያም ቡዝ የወደፊቱ ትውልድ “ሃይማኖት ያለ መንፈስ ቅዱስ፣ ክርስትና ያለ ክርስቶስ ፤ ምህረት ያለ ንሰሐ፣ ድነት ያለ ዳግም ልደት፤ ፖለቲካ ያለ እግዚአብሔር፤ የዘላለም ሕይወትን ያለ ገሃነም እሳት ይሻል” በማለት ትንቢታዊ የሚመሰል ቁምነገር ተናግረዋል። ቦዶ ቤከር የተባሉ የነገረ መለኮት ሰውም፣ በመጨረሻ ዘመን ሰዎች የጨለማ ሥራ አፍቃሪዎች ይሆናሉ በማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አጣቅሰው ሃሳባቸውን ሠንዝረዋል። ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፣(2 ጢሞ. 3፥4- 5)፣ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ይበዛሉ ( 1 ዮሐ.2፥18 ፤ 4፥3)፣ የዋጃቸውን ጌታ ይክዳሉ (2 ጴጥ.2፥1)፣ በጌታ መምጣት ርእስ ላይ ዘባቾች ይሆናሉ፣ አይመጣም በማለት ክደት ይፈጽማሉ (2 ጴጥ.3፥3)፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ (1 ጢሞ.4፥1-2)፣ ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት አይታገሡም (2 ጢሞ. 4፥3)፣ የቅድስና ሕይወትን ይጠላሉ፣ እግዚአብሔር የፈጠረውን መልካም ነገር ይጠየፋሉ (1 ጢሞ. 4፥3-4)፣ ከሰናይ ምግባር ይጎዳላሉ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር የላቸውም (2 ጴጥ. 2፥ 10-12)፣ ከእውነት መንገድ የራቁ ናቸው (2 ጴጥ. 2፥1)፣ እግዚአብሔር አያስፈልገኝም ይላሉ (ራእይ 3፥17)፣ የእግዚአብሔርን ሕልውና ይቃወማሉ፣ ስለ ኢየሱስ ማንነት ልዩ ልዩ ወገኖች የተለያየ ምልከታ አላቸው፣ ኢየሱስ vegetarian ነው በማለት በመብል ዙሪያ ሊገድቡት ይፈልጋሉ፣ የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ (New Age Movement) አራማጆች “ኢየሱስ በውስጡ ያለውን መለኮታዊነት ፈልጎ ያገኘ አስተዋይ ሰው ነው” ይሉታል፣ በሙስሊሞች ዘንድ ኢየሱስ “ነቢይ” ነው፣ በይሓዋ ስምክሮች ዘንድ “የተፈጠረ ፈጣሪ” ነው ፣ ቀደም ሲል ደግሞ ሚካኤል ተብሎ ይጠራ ነበር ይላሉ፣ በሞሮሞሮች ዘንድ በመጀመሪያ ሰው የነበረ፣ ውሎ አድሮ አምላክ መሆን የቻለ ይላሉ፣ ኢየሱስ የአንድ ግብረ ሰናይ አባል የነበረ፣ መልካም ለማድረግ በዘመኑ ጥረት ያደረገ ነው፣ በዘመኑ አብዮተኛ የነበረ፣ ከዘመኑ ሰዎች የላቀ እውቀት የነበረው ነው፤ ሕንዶች ካሉዋቸው ጣኦታት መካከል አንዱ ወይም “አዲሱ ጉሩ” ነው፣ ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ለጠየቃቸው የመለሱትን ለግንዛቤ እነሆ፥ አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ ይሉሃል፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ፣ ከነቢያት አንዱ ነህ ይላሉ በማለት ነገሩት። ኢየሱስ ግን እነርሱ ስለ እሱ የሚያስቡትን ለማወቅ “እናንተስ እኔን ግን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። አስደናቂና አስገራሚ መልስ የሰጠው ሐዋሪያው ጴጥሮስ ነው። “አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰለት። በእርግጥ ይህ ታላቅ መገለጥ ነው። ኢየሱስም ለጴጥሮስ እንዲህ አለው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ብፁህ ነህ፣ ይህን የገልጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም።”(ማቴ. 16፥17) በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ፣ ቤዛ፣ ለኃጢአታችን ሲል ደሙን ያፈሰሰ ጌታ ነው። እርሱ ጌታም ክርስቶስም ነው። ያለ ኢየሱስ ወደ አብ መግባት፣ ስርየት ማግኘትም አይቻልም። “ኢየሱስ፥ እኔ መንገድና እውነት፣ ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ. 14፥6) ይላል!! “መዳን በሌላ በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (ሐዋ. 4፥12)