Created on: 30 December 2024
Description
ትምህርተ ሥላሴ ማወቅ ለምን ያስፈልገናል? ትምህርተ ሥላሴን በተመለከተ የሚቀርቡ ጥያቂዎች፣ ቅዋሜዎች፣ ሙግቶች ብሎም ኑፋቄውያን የቀመሩዋቸው ትምህርቶች ይበልጥ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንማማርና እንድናጠና ግድ ይለናል። ትምህርተ ሥላሴ ዐበይት ከሚባሉት ክርስቲያናዊ ትምህርቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።”ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ባይጠቀስም፣ መሠረታዊ ሃሳቡና ጭብጥ እሳቤዎቹ ጉልህ በሆነ መልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሰዋል፤ተካተዋል።ብሉያትም ሐዲሳትም ይህንኑ እውነት በግልጽ ይነግሩናል። እግዚአብሔር አንድና አንድ ብቻ ነው። ኑፋቄውያኑ ግን ክርስቲያኖች ሦስት አማልክትን ያመልካሉ፣ አንድ አምላክ አያምኑም በማለት ክርክር ያነሳሉ፣ ያቀርባሉ፣ ይሞግታሉ። ሐያሲያን እና ኑፋቄውያን ቤተ ክርስቲያን ሦስት አማልክትን ታመልካለች በማለት ይከራከራሉ፤ እውነትን ከመረዳት ይልቅ በውሸት ፈረስ መጋለብን ይመርጣሉ። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት፣ ቢያንስ በመጀመርያዎቹ አምስት ምእተ ዓመታት የአርዮስና የሰባልዮስ ትምህርቶች ቤተ ክርስቲያንን ተገዳድረው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ምስክር ናችው። በ 325 ዓ.ም. በኒቅያ፣ በ 381 ዓ.ም. በቊስጥንጥንያ፣ በ 431 ዓ.ም. በኤፌሶን፣ በ 451 ዓ.ም. በኬልቄዶን የተካሄዱት የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤዎች በወቅቱ ለተነሱ የመናፍቃን ትምህሮቶች መልስ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ትምህርቶቹን አውግዘዋል፤ ሃይማኖታችንን አጽንተዋል። አባቶች ለመናፍቃን የሰጡት ምላሽና ውሳኔ ዛሬም ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። የመናፍቃኑ ትምህርቶቹ ለብዙ ዓመታት ተዳፍኖ ከቆየ በኃላ፣ በአስራ ዘጠነኛው ክፍል ዘመን ዳግም ማንሰራራት ጀመረ። የይሓዋ ምስክሮች እና የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን (Jesus only) በሚል እራሳቸውን የሰየሙት የአርዮስና የሰባልዮስ ትምህርት ውልዶች ናቸው። በሥላሴ ትምህርት ዙሪያ ያለው ውዥንብር ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ስህተት ትምህርት እንዲያዘንብሉ ምክንያት ሆኑዋል። በቅርብ የማውቀው አንድ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ፓስተር በሥላሴ ትምህርት ላይ ጥያቄዎች እንዳለው የነገረኝን መቼም አልረሳውም። እኔ እራሴ በምሳተፍበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ በዚሁ ርእሰ ዙሪያ ውዝግብ ተነስቶ ነበርና፣ ፓስተሩ እንዲያስረዳና መፍቴም እንዲገኝ ቢጠየቅም፣ ሥላሴን በተመለከተ እኔም ጥያቄዎች አሉኝ በማለት ሳይመጣ ቀረ።ጉዳዩ ዛሬም በሐዘኔታ ይታወሰኛል። በዚህ ትምህርት ዙሪያ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሳይቀሩ መደናገር ይታይባቸዋል። ለዚህ ዐበይ ምክንያቱ የሥላሴ ትምህርት አዘውትሮ ያለመሰጠቱ መሆኑ በብዙ ይገመታል። የካቶሊክ፣ የወንጌላውያን እና የኦሮቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሥላሴ ላይ መሠረተ እምነታቸው አንድና ተመሳሳይ ነው። በጥቅሉ ሲታይ አስተምሆር ሥላሴ በአምስት ዐበይት ነጥቦች ላይ ተመሥርቷል።እነዚህ አምስት ዐቢይት ነጥቦች የትምህርቱ ድርና ማገር አሊያም ምሶሶ ናቸው ማለት ይቻላል። 1. እግዚአብሔር አንድ (አሐዱ) ብቻ ነው፣ ኦሪት ዘዳ. 4፥35፣39 ፤ 32፥39 ፤ኢሳ. 37፥20፤ 43፥10፤ 2 ሳሙ.22፥32፤ ኢሳ.44፥6-8፤ 45፥5፥14፥21-22፤ 46፥9 ፤ ዮሐ.5፥44፤ ሮሜ 3፥30፤ 16፥27፤ 1 ቆሮ.8፥4-6፤ ኤፌ.4፥6 2. አብ ፍጽም አምላክ ነው፣ ዮሐ. 17፥3 1ቆሮ.8፥6 2 ቆሮ. 1፥3 ኤፌ.1፥3 3. ወልድ (ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ) ፍጹም አምላክ ነው፣ ኢስ. 9፥6 ፤ ዮሐ. 1፥1 ፤ 1፥18 ፤ 20፥28 ፤ ሐዋ.20፥28 ፤ ሮሜ 20፥28 ፤ ዕብ.1፥8 4. መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክ ነው፣ ሐዋ. 5፥3-4 ፤ 2 ቆሮ. 3፥17-18 5. አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያየ አካላት አላቸው። ሀ. ኢየሱስ ክርስቶስ አብ አይደለም፣ አብም ወልድ አይደለም፣ ሮሜ. 1፥7 ፤ ዮሐ. 5፥31.32 ፤ 8፥16-18፤ 3፥16-17፤ ገላ.4፥4 ዮሐ.3፥5 ፤ 5፥20 ፤14፥31 ለ. ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ወይም መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፣ ዮሐ. 14፥16 ፤ 1 ዮሐ. 2፥1 ፤ ዮሐ.15፥26 ፤ 16፥7 ፤ 16፥13-14 ሐ. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አይደለም ወይም መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ አይደለም፣ ዮሐ. 14፥15 ፤ 15፥26 ፤ ሮሜ 8፥26-27፤ 28፥29 ከላይ በተጠቀሱት ዐበይት ምክንያቶች የተነሳ የቦን ወንጌላዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ሥላሴ እና ሌሎችንም ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ተከታታይ በሆነ መልኩ ታስተምራለች።